company logo

የራዲዮ ፕሮግራም

Content View Hits : 135568
Home ዜና መግለጫ
መግለጫ PDF Print E-mail
Written by Administrator   
Tuesday, 26 June 2012 03:12

ከኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር/ኢሕአግ/

የተሰጠ መግለጫ

   ዛሬ አገራችን ኢትዮጵያ በጠባብና በጎጠኛው ቡድን ማንአለብኝነት ከድጡ ወደ ማጡ እያመራች ትገኛለች። የገበሬው ዋልታና መከታ ነኝ የሚለው ፋሽስቱ አገዛዝ አርሶ አደሩን ከቀየው በማፈናቀል መሬቱን ለይስሙላው ኢንቨስትመንት ለማስፋፋት እንፈልገዋለን በማለት ነዋሪዎችን መሬት አልባ በማስቀረት እጅና እግራቸውን አጣጥፈው እንዲቀመጡ በጭካኔ ፈርዶባቸዋል።

    አገዛዙ ርካሽ ፍላጎቱን በሕገ-መንግስቱ ስም በሕዝብ ላይ ለመጫን የኢትዮጵያን ህዝብ ታሪክና ጥቅም ባላገናዘበና ህዝብን የማይወክል የውስጥ ግለሰቦች የስልጣንና የመዋዕለነዋይ ጥም ለማርካት ሲባል የተጻፈው ሕገ- መንግስት እንኳን መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን ይግለጽ እንጅ የሃይማኖት ተቋማት ሳይቀሩ የመለስ ቃል አስተጋቢ እንዲሆኑ በተደረገበት ሁኔታ ይህን አንቀበልም ያሉ የሃይማኖት አባቶችን በማሳደድና ጣልቃ በመግባት የተቀደሱ ስፍራዎችን እያረከሱ በሚገኙበት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊት ሃይማኖት አልባውንና ፀረ- ኢትዮጵያ የሆነውን አናሳ ቡድን ላይ ከፍተኛ ወታደራዊ ጥቃት እየፈፀመ እንደሚገኝ ይታወቃል።

   ግንባሩ ባሳለፍናቸው ወራቶችና በያዝነው ሰኔ ወር 2004 ዓ.ም ከወያኔው የመከላከያ፣ የፖሊስ፣ ልዩ ሃይልና የሚሊሻ ጦር ጋር ባካሔደው ድንገተኛ ማጥቃት  በጠገዴ ቀራቅር፣ በታች አርማጭሆ ጫንቃ ወልቃይት አካባቢዎች በወሰዳቸው እርምጃዎች የወያኔን ቅጥረኛ ጦር በመቅጣት ድል መቀዳጀቱ የሚታወስ ነው።

   በተካሄደው  ውጊያ ቆሽቱ ያረረው የወያኔው አገዛዝ ቅጥረኛውን ሰራዊት ክፉኛ በመደቆሱ ምክንያት አገራችን የጀግና ያለህ በምትልበት ወቅት ደማቅ ታሪክ አስመዝግበው ያለፉ ውድ አርበኞች አስከሬን በአደባባይ በመጎተት አስነዋሪ ተግባር በመፈጸም ሌሎች የለውጥ ትግሉን እንዳይቀላቀሉ ለማስፈራሪያነት የተጠቀመበት ስልት መሆኑ ነው።

    ይሁን እንጅ በአንፃሩ የታየውና  እየታየ ያለው የሕዝብ የአልገዛም ባይነት ቁጣ እየጨመረ መምጣቱን የሚያመለክቱ እንቅስቃሴዎች በአርማጭሆ ኮርሁመር፣ ድርማጋ፣ አብርሃጅራ ፣ ሳንጃ የተቃውሞ ሰልፍ  በማድረግ አቤቱታቸውን ለሲቪል አስተዳደሮችና ለጦር መኮንኖች ያስታወቁ ቢሆንም ምላሽ ሲያጡ የክልሉ መስተዳድር የሚገኙበት ባህርዳር በማምራት የመሬት ንጥቂያውን ቢቃወሙም የሰልፍ ትዕይንቱ ያስገኘው መፍትሄ ባለመኖሩ የሰሜን ጎንደር ሕዝብ የቀበሌ መስተዳድር ፅ/ቤቶችንና ፖሊስ ጣቢያ በማጋየት እንዲሁም በግልና በቡድን መሳሪያ እየገዛ ወደ በረሃ እየወጣና ዱር ቤቴ በማለት ከኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊት ጋር እንዲቀላቀል ዋነኛ ምክንያት ከመሆኑም በላይ በጎንደር የዞንና የወረዳ ሹማምንትን በበላይ አለቆቻቸው አማካኝነት እንዴት የሕዝቡን ቁጣ በውድም ይሁን በሃይል ማኮላሸት ይሳናችኋል ? በማለት አስራ ሁለት(12) የሚሆኑ ካድሬዎች ያለምንም ማስጠንቀቂያ ከሃላፊነታቸው እንዲወገዱ ሆኗል። እብሪተኛው ቡድን ያልገባው ነገር ቢኖር በሕዝብ ላይ የሚወሰድ ማንኛውንም አይነት ኢ-ፍትሃዊ እርምጃ የለውጥ ትግሉን ያፋጥነዋል እንጅ ሊያረግበው እንደማይችል ነው።

  አምባገነኖች ውድቀታቸው ሲቃረብ ጆሮዋቸውና አይናቸው ለሌሎች ቦታ አይሰጡም እራሳቸውንና እራሳቸውን ብቻ በማዳመጥ የእውር ድንብር ጉዞአቸውን ቼ! በለው ይሉታል። አምባገነኑ የደርግ አገዛዝ በውድቀቱ ዋዜማ ወቅት በህዝቡ ይወስደው የነበረው  የህይወትና የንብረት ውድመቶች ውድቀቱን ያፋጠኑ እንደነበሩ ልብ ይላል ዛሬም በአገራችን ኢትዮጵያ እየተመለከትን ያለነው ይሔንኑ ሀቅ ነው።

   የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ከወሰዳቸውና እየወሰዳቸው ከሚገኙ ወታደራዊ ጥቃቶች ጎን ለጎን ሕዝቡን የማንቃት የማስታጠቅ ስራዎችንም እያከናወነ ይገኛል። በሕዝቡ በኩል ያለው ምላሽና ድጋፍ እጅግ የሚያበረታታና የሚያጀግን ሆኖ አግኝተነዋል።

   ግንባሩ እንደየወቅቱ ሁኔታ የሚያዘጋጃቸው በራሪ ወረቀቶች በሰሜን ጎንደር ቋራ፣ ወልቃይት፣ ደባርቅና አርማጭሆ የመሳሰሉት አካባቢዎችና በባህርዳር እንዲሁም በመዲናችን አዲስ አበባ በመርካቶ ስድስት ኪሎና ሌሎች ቦታዎች የተበተኑ ሲሆን በተለይም ወጣቱ ክፍል በራሪ ወረቀቶችን በግሉ በማባዛትና በመበተን ረገድ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

  ኢትዮጵያ ውስጥ ላለው ነባራዊ ሁኔታ ከሁለንተናዊ የአርበኝነት ትግል ውጭ አማራጭ አለመኖሩን ሕዝቡ የተስማማበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ኢሕአግ እያካሄደ በሚገኘው የአርበኝነት ትግል ከጊዜ ወደ ጊዜ ተቀባይነቱ እያየለ መምጣቱ አሌ የሚባል አይደለም።

   ድርጅታችን በወያኔ ላይ እየሰነዘራቸው ከሚገኝ ወታደራዊ ጀብድ ባሻገር በአውስትራሊያ፣ አውሮፓና አሜሪካ ኑሮአቸውን በስደት ያደረጉ ኢትዮጵያውያንን በማደራጀቱ በኩል ቀላል የማይባል እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።

   በመጨረሻ የአገሬ ጉዳይ ይመለከተኛል ያገባኛል የምንል ወገኖች ሁሉ ኢሕአግ አምባገነኑን አገዛዝ ከስር መሰረቱ ለማስወገድ ረሃብና ጥሙን ዳገት ቁልቁለቱ ፀሐይ ውሽፍሩን ብሎም ከምንም ነገር በላይ ውድ የሆነችውን አንዲት ህይወቱን ቤዛ በማድረግ አገርና ሕዝቡን ከጥፋት ሃይሎች የመታደግ አኩሪ የትግል ጥሪ ላይ በአገር ውስጥ የምንገኝ ከተቻለ የአርበኞች ግንባርን ሰራዊት በመቀላቀል አገዛዙን በነፍጥ ፊት ለፊት መጋፈጥ አልያም በያለንበት ከግንባሩ ጋር ያለንን ግንኙነት በማጠናከር የሚሰጠንን ተልዕኮ መፈፀምና ማስፈፀም ይኖርብናል።

   በተለያየ የአለም አገራት የምንኖር ኢትዮጵያዊያንም ድርጅታችን ባመቻቸው የውጭ የአሰራር ደንብና ሂደት መሰረት እጃችንን በማስገባት እራሳችንን ከሕሊና እዳ ተጠያቂነት ነፃ የምናደርግበት ወቅት ዛሬ ነው እያልን በወያኔው ላይ እየወሰድን የምንገኘው ተከታታይ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ትግላችን የነፍጥ አምላኪው ቡድን ግብዓተ-መሬት ሳይፈጸም ሊገታ የማይችል ታሪካዊ እርምጃ መሆኑን ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እናስታውቃለን።

                                                            አንድነት ሃይል ነው!!

                                                       ተነስ ! ታጠቅ ! ዝመት!

                                                     የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር/ ኢሕአግ/

                                                             ሰኔ 19-2004 ዓ.ም       

 

 

Search

Latest Articles

  1. 10-09-2005
    (1999-11-30 00:00:00)
  2. 08-09-2005
    (1999-11-30 00:00:00)
  3. 06-09-2005
    (1999-11-30 00:00:00)
  4. 03-09-2005
    (1999-11-30 00:00:00)
  5. 01-09-2005
    (1999-11-30 00:00:00)



Copy right @2010 arbegnochginbar